በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፣ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ

በአባ ገ/ጊዮርጊስ ካሳዬ

ግንቦት 21 2006 ዓ.ም.

ዕርገት የሚለው ቃል መገኛው የግእዝ ቋንቋ ሲሆን፡-

መገኛ ቃሉም “ዐረገ” = “ከፍ አለ፣ ወጣ” የሚለው የግዕዝ ግሥ ይሆናል።

ዕርገት ማለት ደግሞ = ከፍ ማለት፣ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው።

በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ዕርገት ሁለት ዓይነት ነው፡-

የኅሊና ዕርገት እና

የአካል ዕርገት

የኅሊና ዕርገት

ኅሊና ማለት አዋቂ ዕውቀታዊ ልቡና ማለት ሲሆን ሰውን ከእንስሳዊ ፍጡራን ልዩ የሚያደርገው ይኸው ህሊናዊ ዕውቀቱ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከሰማይ በታች ላሉት ፍጥረታት ገዢ ያደረገው ኅሊናም፣ እውቀትም ሰጥቶ ነው። ይህ ራሱንም ሆነ ዓለምን የሚያስተዳድርበት ብቁ ኅሊናዊ እውቀት ነው። ሰው አምላኩን እግዚአበሔርን አውቆ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርጎ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ፣ ለማክበር፣ ለመፈጸም በእሳቤው ከፍታ ላይ ሲደርስ “ዐርገ ዲበ ኅሊናሁ ከመ ይግበር” ማለትም “ሥራን ይሠራ ዘንድ ወደ ኅሊናው አርጓል” ይባላል። ለምሳሌ፦ ሄኖክ በእምነት፣ ኤልያስ በአምልኮት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በስብከት፣ ቅዱስ ጳውሎስ በምስጢራት የዕርገት ኅሊና ባለቤቶች ሆነዋል።

የኅሊና ዕረገት በፍጹም ተመስጦ ሆኖ ነገረ እግዚአብሔርን፣ የእግዚአብሔርን ሥራ፣ ነገረ ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ ስቅለቱን፣ ትንሣኤውን፣ እርገቱን፣ እንዲሁም ዳግም ምጽአቱን  ማሰብ፣ መመርመር ነው – እንደ አባ ሕርያቆስ – “ወሶበ እሔሊ ዘንተ ይፈቅድ ሕሊናየ ይዕርግ ላዕለ ወይጸዐን በመትከፈ ነፋሳት ወይሥርር … ይርዓይ ህላዌሆሙ ለፍጡራን … ዕመቃቲሆሙ ለአብሕርት ያእምር ሉዓሌሁ ለሰማይ” እንዳለ። “ይህንን ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ በነፋስ ትከሻ ተጭኖ ወጥቶ የፍጡራንን አኗኗር የአብሕርትን ጥልቅነት የሰማዩን ርዝመት ያውቅ ዘንድ ይወዳል ግን አቅቶት ይመለሳል”። ቅዳሴ ማርያም ቁ. 86

በቅዳሴ ጊዜም ኅሊናችን ከፍ ከፍ እንዲል ካህኑ “አልዕሉ አልባቢክሙ” – “ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” ይለናል። ሕዝቡም ይህን ተከትሎ “ብነ ሀበ እግዚአብሔር አምላክነ” – “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን፤ ልቡናችንን ወደ አምላካችን እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አድርገናል ይላል። ይህ ሁሉ የኅሊናን ከፍ ከፍ ማለት፣ ዕርገተ ኅሊናን ያጠይቃል (ያስረዳል)።

የአካል ዕርገት

የአካል ዕርገት ዝቅተኛ ቦታ ላይ ኖሮ ወደ ከፍተኛው ቦታ መውጣትን ከፍ ማለትን ያሳያል። በዚህ ምድር ሆነው እጅጉን እግዚአብሔርን የወደዱትን ከፍ አድርጎ አሳረጋቸው። ለዚህም ሔኖክና ኤልያስን አብነት እናደርጋለን።

ሰው የተፈጠረው፣ አምላኩን እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ ለመታዘዝ ሆኖ ባለመታዘዙ ምክንያት ወደቀ። ከድቀቱ ያነሳው ዘንድ አምላክ ወልደ አምላክ ሰው ሆኖ ተገለጠ። የማይታየው አምላክ በሥጋዌው (ሰው በመሆኑ) ታዬ። የመምጣቱ፣ የመገለጡ ተቀዳሚ ዓላማ የወደቀውን የሰው ልጅ ማንሳት ነውና። ውድቀት ምንድን ነው?

ከእግዚብሔር መለየት ነው፦ በኃጢያት ምክንያት።

በልዩ ልዩ ደዌ ሥጋ መያዝ ነው።

በነፍስ ባርነት በሲኦል መጣል ነውአግብርተ ዲያቢሎስ (የዲያብሎስ ተገዥዎች) መሆን ማለት ነው።

መሐሪ ይቅር ባይ አምላካችን በኃጢያት ለወደቀው የሰው ልጅ በንስሐ እንዲመለስና በፍጹም ልቡ እንዲያምን፣ በጥምቀትም ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅነትን እንዲቀበል ይህን የልጅነት መብት ሰጠው። “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን።” 1ኛ ዮሐ 3፥1። “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” ዮሐ 1፥12-13።

በደዌ ሥጋ የተያዙትንም እንዲሁ ፈወሳቸው፤ አዳናቸው። ለአብነትም፦ መፃጉዕን ፈወሰ ዮሐ 5፥1፤ እውር ሆኖ የተወለደውን ብርሃን ሰጠ ዮሐ 9፥1 – ፍጻሜ፤ አሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት ፈወ ማቴ 9፥20-23። ደግሞም በዚህ ሳይወሰን አልአዛርን ከሙታን አስነሳ ዮሐ11፥43-44።

ነፍስ ባርነት ዳግም እንዳንያዝ ነፃ ያወጣን ዘንድ የዕዳ ደብዳቤያችንን ቀደደ፤ ስለፈጸምነው የኃጢያት በደል ዕዳችንን ይከፍል ዘንድ መስቀል ተሸከ ቀራንዮ ወጣ። “ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ።” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ቆላ 1፥20። ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦሥተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። ሞትን ገደለው፤ በሲኦል ለነበሩት ነፍሳትም ነፃነትን ሰበከላቸው፤ ከትንሳኤው በኋላ ከእርገቱ አስቀድሞ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሥርዓትን አስተማራቸው (መጽሐፈ ኪዳን)፤ በ40ኛውም ቀን ዐረገ። “እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።” ሉቃ 24፥51-52። ማር 16፥19። ሐዋ 1፥9-11።

የጌታችንን ዕርገት ከቅዱሳን ከእነ ሔኖክና ኤልያስ ዕርገት ሲለይ ወንጌል እንዲህ ይላል “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም።” ዮሐ 3፥13። “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።” ማር 16፥19። ዐረገ የተባለው እኛን የመሰለበትን ከእመቤታችን የነሳውን የነፍስ የሥጋ ባሕርይ እንጂ በመለኮቱማ ጥንቱንም ቢሆን ከአብ እሪና አልተለየም። በየማነ አብ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥን ገንዘብ አደረገ የምንለው ትስብእትን (ሥጋን) ነው። “ዐርገ ነሢኦ ሥጋ እንተ እምኀቤነ ተለዓለ ተሰብሐ እምኀበ አቡሁ” – “ከእኛ በነሳው ሥጋ ዐረገ በአባቱም ዘንድ ተመሰገነ።” “ሎቱ ስብሐት ወሎቱ አኮቴት ወሎቱ ይስግዱ መላእክት ወኩሉ ፍጥረት ሎቱ ይትቀነዩ መላእክት” – “ለእርሱ ምስጋና ክብር ስግደት ያቀርቡለታል ፍጥረታትም ሁሉ ለእርሱ ይገዙለታል”። እንዳለ ቅዱስ ያሬድ።

ዕርገተ ክርስቶስ አስቀድሞ በነቢያት የተተነበየ በወንጌል የተሰበከ በሐዋርያት እና በኋላም በተነሱ ሊቃውንት በስፋት የተነገረለት ነው። ለአብነት ያክል በጥቂቱ ብንመለከት:-

ትንቢት፡-

“ዐርገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ” – “ምርኮን ማርከህ ዐረግህ።” መዝ 67፥18። የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ዋና ዓላማውም የሰውን ልጅ ማዳን ነበርና ምርኮን ማርከህ የተባለው አዳምንና ልጆቹን ከኃጢያት ከፍዳ ነፃ አውጥቶ የራሱ ገንዘቦች አድርጎ ዐረገ ማለት የአዳም አካል በአብ እሪና መቀመጥ አዳምና ልጆቹ የእግዚአብሔር እርስት ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው። ጠላት ዲያብሎስ በእኛ ምንም ቦታ ላይኖረው አደረገው። “ጸርሐ ገብርኤል እምሰማይ ወይብል፥ ፃዑ ተቀበሉ መጽአ ወልደ አምላክ በለቢሰ ሥጋ ማርያም ወፄዊዎ ነፍሳተ ዓለም።” – “ገብርኤልም ድምጹን አሰምቶ ተናገረ ትቀበሉ ዘንድ ውጡ የአምላክ ልጅ የማርያምን ሥጋ በመልበስ የዓለምን ነፍሳት ማርኮ መጥቷልና።” እንዲል።

“አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ።” መዝ 46፥5-6

ወንጌል፡-

“በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤” ዮሐ 14፥2።

“ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።” ማር 16፥19። ሉቃ 24፥51-52። 

ቅዱሳን ሐዋርያት/አርድእት፡-

“ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” ሐዋ 1፥9-11።

“እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።” 1ኛ ጢሞ 3፥16

ሊቃውንት፡-

“ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ” – “በምስጋና ወደ ሰማይ አረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ”። ጸሎተ ሃይማኖት ዘሠለስቱ ምዕት

“በቀኜም ተቀመጥ አለው ይህ ሥጋ ቀድሞ አንተ መሬት ነህ ወደ መሬትነትህም ትመለሳለህ የሚል አዋጅ ሰምቶ ነበር። ዛሬ ግን ለዚህ ሥጋ ከሰማያት በላይ መሆን ብቻ አልበቃውም፥ በመላእክት ቦታ አልተወሰነም። ይህም ክብር አልበቃውም። ከመላእክት በላይ ሆነ ከሱራፌልም በላይ ከፍ አለ ወጥቶ ከሊቃነ መላእክት በላይ ሆነ እንጂ ወደላይ መውጣት ብቻ አልበቃውም ወደ መንግስት ዙፋን ወጥቶ በላይ እስከመቀመጥ ደረሰ እንጂ።” ሃይ.አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም 68፥24

እንግዲህስ ለክርስቲያን የሚገባው ይህን ማወቅና መረዳት ማመንና መኖር ነው። “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህቺ የዘለዓለም ሕይወት ናት።” ዮሐ 17፥3።

ጌታችን እና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ዕርገት ስናከብር ስለ እኛ በኃጢያተኞች እጅ ተላልፎ መሰጠቱን፥ ስለበደላችን ካሳ መክፈሉን፥ እንድንበት ዘንድ ስለ እኛ ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን፥ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሕቱም መቃብር መነሳቱን፥ በአርባኛውም ቀን ማረጉን እያሰብን በዕርገተ ኅሊና ሆነን፥ ከዚህ ዓለም ከንቱ አስተሳሰብ እርቀን ሊሆን ይገባል። ቅዱሳን መላእክት ለሐዋርያት እንደነገሯቸው ጌታችን በሥጋ ማርያም በክብር እንዳረገ እንዲሁም በግርማ መለኮት በክበብ ትስብእት (በሥጋ ማርያም) በዳግም ምጽዓት ተመልሶ ይመጣል። “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” ሐዋ 1፥9-11።

ስለዚህም ጌታችን ለፍርድ ሲመጣ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ከሚላቸው እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን እየተቀበልን በእርገተ ኅሊና ሆነን ልንኖር ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

{flike}{plusone}