አንግሰነው መጣን

 ከፅዮን ጌታቸው

አንግሰነው መጣን ቅዱስ ኡራዔልን

የተቦሪ ካሉት ወገኖች ጋር አብረን

መንፈስን የሚያድስ ጊዜን አሳልፈን

በደስታ በፍቅር በአንድነት ሆነን

   ተሰባሰብንና አርብ ከሰአት

   እመሃል ከተማ ተቃጠርንበት

በጸሎት ጀመርነው መንገዳችንን

አምላክ በቸርነት በሰላም አድርሶ እንዲመልሰን

   ፍቅራችን ሲያስደስት እንዲሁ ዝማሬያችን

   ስናደርስ ምስጋና ለቸሩ አምላካችን

በመሃሉም አረፍ አልንና ለምሳ

ከወደ አገልግሉ ምግብ ልናነሳ

ቀዩን ከአልጫው እንዲሁም ለስላሳ

ተበላ ተጠጣ ታጅቦ በጉርሻ

ተመልሰን ገባን ወደ መንገዳችን

ለደካማዉ ስጋ ትንሽ ጉልበት ሰተን

እኩለ ለሊት ላይ ደረስን ከደጁ

ከሰላሙ መላክ ከቅዱስ ዑራዔል ከወደ አማላጁ

   ሲጠብቁን ነበር በናፍቆት በደስታ

   ተቀበሉን ወተዉ በዝማሬ በእልልታ

   ምግብም ቀረበልን ማረፊያ መኝታ

ድካማችን አልፎ ነቃን በጠዋት

በመቅደስ ተገኝተን በነግህ ጸሎት

በታምር በኪዳን በቅዳሴዉ ስርአት

ሁሉንም ፈጽመን በአባቶች መሪነት

     በአጥንት አለምላሚው ህጻናት አንደበት

     በመዘምራኑ በወጣት ባዛውንት

   ሰአቱ ደረሰ የምንዘምርበት

   እንደመላእክቱ ለአምላክ ስብሃት

     በአንድነት ሆነን የምናቀርብበት

እንደተለመደው አስተማሩን አባ

እንድንጾም እንድንጸልይ ንስሃ እንድንገባ  

አንተ ትብስ አንቺ ሁሉ ተባብሎ

ፍቅርን ተላብሶ ክርስቶስን መስሎ

ተጉዞ ባንድነት ፍኖተ ህይወት

በስጋ ወደሙ ከብሮ እንዲኖርበት

ብሎም ያቺን መንግስት እንድንወርሳት

ህዝቡም ታዛዥ ነበር ላስራት በኩራት

ሁሉ ተሳተፈ ብር በማዋጣት

   እንዲህ እንዲያ እያልን ሁሉንም አድርሰን

      በመዝሙር በእልልታ ታቦቱን አንግሰን

     በወረብ በዝማሬ መልአኩን አክብረን

     ዝማሬው ባያልቅም ሰአት ቢገድበን

     እንደዛሬው ሁሉ ላመቱ እንዲያደርሰን

     ለጊዜው አቆምን ያብጸሃነ ብለን

      ወደተዘጋጀው ወደ ምሳው ሄድን

 አቤት መጣፈጡ የቀረበዉ ምግብ

   ደግሞ ትህትናቸው የሚያሳዩን ክብር

 ሁሌም በመጣሁኝ ያሰኛል ፍቅራቸው

 መቼ ይሆን ኡራኤል ቀጥሎ ሚነግሰው?

   ብሎ እነዳስጠየቀን ማን በነገራቸው

     ተሰነባበትን ሰአቱ ደረሰና

     ድጋሜ ለመምጣት ቃልም ገባንና

ወጣን ካዉቶቢሱ ታስሮልን አገልግል

ሳይደክመን በርትተን መድረስ እንድንችል

በጸሎት ጀመርነዉ ጉዞ ወደቤታችን

አረፍ አረፍ ብለን በየወንበራችን

ምስጋናዉ ቀጠለ ለአምላክ በዝማሬ

እንዲሁም ለድንግል እሙ ለፈጣሪ

ጻድቃን ሰማእታት ሁሉንም አድርሰን

በእልልታ ጭብጨባ ከበሮ እየመታን

   የጥያቄና መልስ ዉድድርም ነበር

   እዉቀት እሚያሰፋ እምነት የሚጨምር

   ሁሉም እንደየ አቅሙ ሊመልስ ሲሞክር

   የህጻናት ተሳትፎም ጎልቶ ይታይ ነበር

ምኑንም ሳናውቀው ነበር የደረስነው

Stocholm Central የሚል ጽሁፍ ያየነው

ይመስገን ፈጣሪ ቸሩ አምላካችን

ይህን የመሰለ ብሩክ ቀን ለሰጠን

በሰላም አድርሶ በቸር ለመለሰን።       

           ወስብሃት ለእግዚአብሔር