ሆሣዕና (የዐቢይ ጾም 8ኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሴት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡

ትርጉም: “በፋሲካ በዓል ሰሞን የእውነት አምላክ ደቀ መዛሙርት ወደ ደብረ ዘይት ቀረቡ፤ በሀገረ እግዚአብሔር (ኢየሩሳሌም) አቀበቱ ላይ ብዙ አረጋውያንና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፣ በአህያ ውርንጫ ላይ ተጭኖ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ለእነዚህ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።

መልዕክታት

ዕብ.8÷1-ፍጻ. ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት፡፡

1ኛጴጥ.1÷13ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡    

የሐዋ.8÷26-ፍጻ. የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው÷ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ፡፡” ተነሥቶም ሄደ፡፡” እሆም÷

 

ምስባክ

መዝ.80÷3 “ንፍሑ ቀርነ በዕለት ሠርቅ፡፡ በእምርት ዕለት በዓልነ፡፡ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ”         

ትርጉም፦ በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና÷ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ ነውና፡፡

ወይም

መዝ.80÷2 “እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡”

ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፡፡ ስለ ጠላት÷ ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡

ወንጌል

ዮሐ.12÷1-11 ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ፡፡

ቅዳሴ ዘጎርጎርዮስ፡፡