የአጥቢያው የመተዳደርያ ደንብ ጸድቆ በሥራ ላይ ዋለ

የስቶክሆልም መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የመተዳደርያ ደንብ ረቂቅ በሀ/ስብከቱ ታይቶ እና ታርሞ በሥራ ላይ እንዲውል ተፈቀደ።

የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኗን የአገልግሎት አድማስ ማስፋት እና ማስቀጠል እንዲቻል ዋናው ቃለ ዓዋዲ በሚገባ ተጠብቆ፤ ይህ አጥቢያው የሚመራበት የመተዳደሪያ ደንብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት ሳይወጣ አጥቢያው የተመሠረተበትን ሀገር አሠራር እና ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተዘጋጅቷል። የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ የመተዳደርያ ደንቡን ረቂቅ ለአጥቢያው ማኅበረ ምእመናን ጠቅላላ ጉባኤ አቅርቦ ሠፋ ያለ ውይይት እንዲካሄድበት ካደረገ በኋላ የተሰጡ አስተያየቶች እና ማሻሻያዎች ተካተው የተሻሻለውን ረቂቅ ሀገረ ስብከቱ በጉባኤ አይቶ እና አስተካክሎ እንዲያጸድቀው መላኩ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ሀ/ስብከቱ ረቂቅ ደንቡን ተመልክቶ አስፈላጊውን ማሻሻያ ካደረገ በኋላ በሥራ ላይ እንዲውል ፈቅዷል።

እሑድ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ በደብሩ አስተዳዳሪ በመላክ ብርሃን አባ ገ/ጊዮርጊስ አማካይነት በተነበበው የሀ/ስብከቱ የመሸኛ ደብዳቤ ”… ደንቡ በሥራ ላይ እንዲውል የተፈቀደ መሆኑን እየገለጽን የደብሩ ሰላምና የሕዝበ ክርስቲያኑ ፍቅር፣ አንድነት እንደተጠበቀ በደብሩ የሚሰጠው ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጋር እናሳስባልን።” ሲሉ የመላው አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል።

የጸደቀውን የመተዳደርያ ደንብ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ