ሞተ ወልደ እግዚአብሔር

ፈጣሪዋ በዕንጨት መስቀል ላይ ተዘርግቶ ተሰቅሎ በአየችው ጊዜ ፀሐይ ጨለመች እርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም14 የነሣትን ለባዊት ነባቢት የሆነች ነፍሱን ከሥጋው ለያት ሐዋርያ ጴጥሮስ በሥጋ ምውት ሲሆን በመለኮት ሕያው ነው እንዳለ ነፍሱ ከመለኮት ሳትለይ ከሥጋ ተለየች በዚያ ጊዜ ሥጋ ከመለኮት ሳይለይ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር፡፡

እንዲሁም ነፍስ ከመለኮት ጋራ አንድ ሁና እሥረኞች ነፍሳትን ትፈታቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች፡፡

እርሱ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ ያለ ልዑለ ባሕርይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ ያለ ለእርሱም ምስጋና የክብር ክብር ገንዘቡ የሆነ ራሱን ሠውቶ አዳነን፣ የመንግስቱን ደጆች በፈሳሽ ደሙ ከፈተልን፡፡

ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለ የእግዚአብሔር ታላቅ የማዳን ሥራ ለባሕርያዊ ደግነቱ የተገባ ነው፡፡ አንድ ንጉሥ የመሠረተው ከተማ ወይም የሠራው ቤት ከጠባቂዎቹ ስንፍና የተነሣ በሽፍታ ቢጠቃና ቢወረር ሽፍታውን ተበቅሎ ይዞታነቱን ያጸናል እንጂ በጠላት በመወረሩ ምክንያት አይተወውም፡፡ የአብ አካላዊ ቃልም የእጁ ሥራ የሆነውን የሰው ዘር ጠፍቶ እንዲቀር አልተወውም፤ ሞትን የራሱን ሰውነት ለሞት አሳልፎ በመስጠት ሲያስወግድ፣ ለሰው ተሰጥቶት፣ ነገር ግን ሕጉን በመተላለፉ ምክንያት አጥቶት የነበረውን ሁሉ በኃይሉና በሥልጣኑ መለሰ፡፡

ይህንንም በመንፈሰ እግዚአብሔር የተቃኙት የመድኀኒታችን አገልጋዮች የጻፏቸው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ በማለት ያረጋግጡልናል፡፡ ‹‹ይህን ስለ ቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፣ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፣ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡›› 2 ቆሮ 5÷14-15

በመቀጠልም ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ የእግዚአብሔር ቃል ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ምክንያቱን ይነግረናል፡- ‹‹ሁሉ ለእርሱ የሆነና ሁሉም በእርሱ ለሆነ ለርእሱ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ተገብቶታልና፡፡›› ዕብ. 2÷9 ይህም ማለት ሰውን ከጀመረው ጥፋት መልሶ ሕይወትን መስጠት ጥንቱን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ቃል በስተቀር ለሌላ ለማንም ተገቢ አይደለምና፡፡

አካላዊ ቃል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደው እንደ እርሱ ሰዎች ለሆኑ ሥጋውያን ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ ነበር፡፡ ሐዋርያው ‹‹ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱም እንዲሁ በሥጋና በደም ተካፈለ፤ በሞቱ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ይሽረው ዘንድ፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፤ በሕይወታቸው ዘመን ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ ያወጣ ዘንድ›› ዕብ. 2÷14-15 በማለት እንደገለጸው፡፡ የራሱን ሰውነት በመሰዋት በእኛ ላይ የነበረውን ሕግ (ትሞታለህ የሚለውን) በመፈጸም አስወገደልን፡፡

 

እርሱ ራሱ በእኛ ላይ የነበረውን እርግማን ሊያስወግድ ከመጣ ለእርግማን የተቀመጠውን ሞት ካልተቀበለ በስተቀር እርግማናችንን እንዴት አድርጎ ይሸምልን ነበር? ይኸውም መስቀል ነው፡፡ ሰውም ሕጉን በተላለፈ ጊዜ ስለ ተረገመ የዚህ ርግመት ካሣ ሊከፈል የሚችለው የርግመት መገለጫ የሆነውን የመስቀል ሞት በመቀበል በመሆኑ ጌታችን የመስቀል ሞተ ተቀበለልን፡፡ ‹‹በእንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፡፡›› ገላ. 3÷13 ተብሎ እንደተጻፈ፡፡

የሁላችን መድኀኒት ስለ እኛ ሞቶልናልና በእርሱ የምናምን እኛ በሕግ መልክ በማስጠንቀቂያ በተነገረውና ባጠፋን ጊዜም በተግባር በደረሰብን (በተፈጸመብን) የሞት ፍርድ እንደ ቀድሞው በኩነኔ ሞት አንሞትም፡፡ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞትን ተቀብሎ የሕግ አፍራሽነት ዕዳችንን ከከፈለልን በኋላ ይህ ፍርድ ተፈጽሞ አልቋልና፡፡ እንዲሁም ሙስናና ጥፋት በጌታችን የትንሣኤ ኃይል ስለ ተወገደ ዛሬ እኛ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ የምንሞተው ለሰውነታችን ተፈጥሮ እንደሞስማማ ሞተን የበለጠውን ትንሣኤ እናገኝ ዘንድ ነው፡፡

ደግሞም የጌታችን ሞት ለሁሉም ቤዛ ለመሆንና ሁሉንም ለመቤዠት እስከሆነ ድረስና በሞቱም የጥል ግድግዳን ያፈርስ ዘንድ፣ አሕዛብን ይጠራ ዘንድ እንደመሆኑ መጠን በመስቀል ላይ ባይሰቀል ኖሮ እንዴት ወደ እርሱ ይጠራን ነበር? ሰው እጆቹ ተዘርግተው ሊሞት የሚችለው በመስቀል ላይ ብቻ ነውና፡፡ በአንድ እጁ ቀደምት ሕዝቡን (አይሁድን)፣ በሌላው እጁ ደግሞ አሕዛብን ይጠራ ዘንድ ሁለቱንም በእርሱ አንድ አድረጎ ያዋሕዳቸው ዘንድ ጌታችን እጆቹን ዘርግቶ በመስቀል ላይ ሊሞት ተገባው፡፡ በምን ዓይነት ሞት ዓለሙን እንደሚቤዥ ሲያመለክት እርሱ ራሱ ያለው እንዲህ ነውና፡-‹‹እኔ ከምድር ከፍ ባልሁ ጊዜ ሁሉንም ወደ እኔ እስባለሁ››፡፡ እንዲሁም ጌታችን የመጣው ሰይጣንን ድል ለማድረግና ዕንቅፋትነቱን ከመንገዳችን ለማስወገድ፣ አየራትን ለማዘጋጀት ነውና፡፡ ይህስ ከምድር ከፍ ብሎ በአየር ላይ ከሚፈጸም ሞት ማለትም ከመስቀል ሞት በስተቀር በምን ዓይነት ሞት ሊፈጸም ይችል ነበር? በአየር ላይ ሊሞት የሚችለው በመስቀል ላይ የተሰቀለ ብቻ ነውና፡፡


ሰላም ለሕማማቲከ በተጸፍዖ መልታሕት ከመ እቡስ፡፡ በተቀሥፎ ዘባን ዓዲ ወተኰርዖ ርእስ፡፡ እንዘ መላኪሆሙ አንተ እግዚአብሔር ንጉሥ፡፡ ኢያፍርሁኒ ቀታልያኒሃ ለነፍስ፡፡ እስመ ማኅተምየ ደምከ ቅዱስ፡፡

ምንጭ፡- ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ግንቦት 2000 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ
መጽሐፈ ስንክሳር በግዕዝና በአማርኛ፣ ከመጋቢት እስከ ጳጉሜን፣ ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፣  1993 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ