ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ

ጥር 8 ቀን 2007 ..

በመልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ 

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ

 

Timketወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ” – ”ዳግመኛ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ወለደን”

”ወለደነ ዳግመ” - ”ዳግመኛ ወለደን” ሲል የልደትን ሁለትነት ያሳያል። የመጀመሪያው ልደት የአዳም ጥንተ ተፈጥሮ ሲሆን፣ ሁለተኛው ልደት ከው ከመንፈስ ቅዱስ የተወለድነው ልደት ነው። ቀዳማዊ ልደታችን ወይም ተፈጥሮአችን ጥልቅ እንደሆነ ሁሉ፤ የሁለተኛው ልደታችንም የማይመረመር ምሥጢር በመሆኑ ምሥጢረ ጥምቀት ተብሏል። ለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እርሱ ለመጣው ለአይሑድ መምህር ለኒቆዲሞስ ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳልና ድምጹን ትሰማለህ እንጂ ከየት እንደሚመጣ ወዴት እንደሚሔድም አታውቅም፤ ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለድ ሁሉ እንዲሁ ነው። በማለት የዳግም ልደታችንን ረቂቅነት አስረድቶታል። (ዮሐ 3፥8) ልደት ቀዳማዊ ተአውቀ በደኃራዊ” – የመጀመሪያው ልደት በሁለተኛው ታወቀ” እንዲል።

ሁሉን ቻይ አምላክ አባታችን አዳምን በግብር አምላካዊ እንደ እርሱ ያለ ሳይኖር ካለመኖር ወደ መኖር በመልኩ፣ በአርዓያው፣ በምሳሌው አድርጐ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም ከው ከመሬት፣ ከነፋስና፣ ከእሳት  ፈጥሮ፤  የተፈጥሮአችን ተጠባቢ እርሱ ነውና፣ ለባዊት፣ ነባቢትሕያዊት ነፍስን ሰጥቶ (”ወነፍሓ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈሰ ሕይወት እንዲል) በቸርነቱ፣ በምሕረቱ ልደት ቀዳማዊን አድሎ፣ አካለ ሥጋን ከአካለ ነፍስ ጋር አዋሕዶ አክብሮ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ አድርጐ በገነት አኖረው። (ዘፍ 27-15)

ነገር ግን አዳም የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመጠበቁና ለፈቃደ ሥጋው በመገዛቱ ከፈጣሪው ጋር ተጣላ የተሰጠውን ጸጋውን ሐብቱን አጣ ከገነት ወጣ ምድረ ፋይድ ወረደ። ገዥው ያልነበረ ገዛው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብሎ ስመ ግብርናት (የባርነት ውል) ሰጠ። የተጻፈውም ውል ጠላት በወደደው ነውና በወረቀት ብጽፈው ይጠፋል በእንጨት ብጽፈው ይበሰብሳል ብሎ በዕብነ ሩካብ ወይም በዕብነ በረድ ጽፎ አስፈርሞ የራሱ ድርሻ በሲኦል የአዳም ድርሻ በዮርዳኖስ ጥሎታል። የባርነቱን ውል መሠረት አድርጎ በልዩ ልዩ ምክንያት የሰውን ልጅ ኃጢአት እያሠራ ከፈጣሪው ጋር እያጣላ ሲያስቀስፈው ኖሯል። ለምሳሌ ማየ አይኅ (የጥፋት ውኃ) እሳተ ሰዶም፣ ስብኮ ላህም (የሲናው አምልኮ ጣዖት) በወቅቱ የነበሩትን ሰዎች ለጥፋት አብቅቷቸዋል።

እሥራኤል ምድረ ርስት ገብተው እግዚአብሔርን ፈርተው ቤተ መቅደስ ሠርተው ጠላት ጠፍቶላቸው ተዘልለው ሲኖሩ፣ ሰይጣን ከእግዚአብሔ የተሰጣቸውን ሕጉን ሥርዓቱን አፍርሰው ለአምልኮ ጣዖት እንዲገዙ ልጆቻቸው ሳይቀር ለጣዖቱ እንዲገብሩ በማድረጉ በነቢያት ተወቅሰዋል በአሕዛብ ነገሥታት ተቀጥቅጠዋል። ነገር ግን ሰው ወዳጅ ይቅር ባይ እግዚአብሔር ለአባታችን አዳም በሰጠው ተስፋ በአምስት ቀን ተኩል አድንኃለሁ ባለው መሠረት እንዲሁም በነቢያት አድሮ በዕለት ኅሪት ሰማዕኩከ ወበዕለተ መድኒት ረዳእኩከ” – ”በተመረጠች በተወደደች ዕለት ሰማሁህ በመድኃኒት ቀንም ረዳሁህ” (ኢሳ 49፥ 8) እንዳለው የጠላትን ተንኮል ከንቱ ያደርግ ዘንድ፦

vሰው ሆኖ ተገለጠ:-

  Øወአመ በጽሐ ዘመነ ሣህል ፈነወ ወልዶ ከመ ይሠጎ - የይቅርታ ዘመን በደረሰ ጊዜ ልጁ ሰው ሆኖ ይገለጥ ዘንድ ላከው።

  Øተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል ኮነ ብእሴ። - ከመንፈስ ቅዱስ ግብር የተነሣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተገለጠ። እንዳሉ ሰለስቱ ምዕት

vበሠላሳ ዘመኑ ተጠመቀ:-

  Øበቤተልሔም ተወለደ በየጥቂቱም አደገ በግልጥ ተመላለሰ እንደ ሰውም ታየ በየጥቂቱ አደገ በሠላሳ ዘመን በዮርዳኖስ ተጠመቀ እንዳለ ዲዮስቆሮስ።

  Øበጊዜው በዘመኑ ሁሉ ከአብ ጋር ትክክል የባሕርይ አምላክ ሲሆን ሰው እንደ መሆኑ በሥጋ አካል በየጥቂቱ አደገ በመለኮቱ ፍጥረትን ሁሉ የሚያከብር ሲሆን ለሰው እንደ ሚገባ በዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ እንዳለ ቄርሎስ በሃይ አበው ም70 ቁ26።

  Øየሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት ተገለጠ ”ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” (ማቴ 3፥16-17)

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ዓመቱ የመጠመቁ ዋና ዓላማ አባታችን አዳም የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ የተሰጠውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና በጥምቀት ወይም በዳግም ልደት ልጅነቱን ይመልስለት ዘንድ ተጠመቀ። በዮርዳኖስ የተጣለውን የባርነት ደብዳቤአችንንም ይደመስስልን ዘንድ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ አደረገው። ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርዐቱ እምዕድውነ ወአዕተቶ እማዕከሌነ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ደብዳቤአችንን ደመሰሰልን (ቆላ 2፥14) ይኸውም የተደረገልን በጽድቅ ሥራችን እንዳልሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጥን ወአኮ በምግባረ ጽድቅነ ዳዕሙ በምሕረቱ አድኀነነ በጥምቀተ ዳግም ልደት ወተሐድሶ በመንፈስ ቅዱስ።” በጽድቅ ሥራችን አይደለም በምህረቱ አዳነን እንጂ ዳግም ልደትን በመንፈስ ቅዱስ መታደስንም በሚያሰጥ ጥምቀት። ብሎአል። (ቲቶ 3፥5)

ጥምቀት ዳግም የተወለድንበት ምሥጢር ነው። የተፈጥሮአችን ተጠባቢ እርሱ እንደሆነ ሁሉ የዳግም ልደታችን ተጠባቢም እርሱ ነውና ጌታችን ጥምቀትን ስለ እኛ መሠረተልን። ስለዚህም ከአባት ከእናት ለተወለድንበት ሥጋዊ ልደት ጥምቀታችን ዳግም ልደት ተብሏል ዳግመኛም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሁለተኛ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት አትችሉም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውናእንዳለን ጌታ በወንጌሉ (ዮሐ 3፥5-6) የሥጋ ልደት ማለት ለተገኘንበት አካል መስሎ አሕሎ መቆም ነው።  አዳም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ በግብር በመልክ የሚመስለውን ልጅ ወለደ። ተብሎ እንደተጻፈልን። (ዘፍ 5፥3) እኛም በጥምቀት የተሰጠችን ልጅነት ፍጹም አባታችንን የምታስመስለን ናት:- ውም ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ሲል በሕያው ቃሉ አረጋግጦልናል። (ዮሐ 3፥6)

ወንጌላዊ ዮሐስም የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ አብ የሰጠን ፍቅሩ እንዴት እንደሆነ ልጆቹም እንደሆን ዕወቁ ብሎናል። (1ኛ ዮሐ 3፥1)። እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እናንተ የእግዚአብሔር ማደሪያዎች እንደ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን? ... እንግዲያውስ የእግዚአብሔር ቤቱ ቅዱስ ነውና የእግዚአብሔን ቤት አታርክሱ። በማለት ከመንፈስ ቅዱስ መወለዳችን ብቻ ሳይሆን እኛነታችን፣ በእኛ ያለው አካል የእግዚአብሔር እንደሆነ ገልጦ አስተምሮናል። (1ኛ ቆሮ 3 ፥ 16-17)

ስለዚህ እኛም በየዓመቱ እንደምናደርገው ሁሉ የጥምቀትን በዓል ስናከብር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ሊያወጣን፣ የዕዳ ደብዳቤአችንን ሊደመስስልን፣ እርሱ መምህረ ትህትና ሆኖ በባርያው በአገልጋዩ እጅ እንደተጠመቀ እያሰብን፣ የተሰጠንን ሐብተ ውልድና ስመ ክርስትና ጠብቀን እርሱ እንደ ወደደን እኛም እርስ በርሳችን በመዋደድ በሰማይ ላለ አባታችሁ ልጆቹ ትሆኑ ዘንድ ይቅር ባዮች ሁኑ እንደተባልን ይቅር በማለት ሊሆን ይገባል

ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም የምንወለድበትን ረቂቁን ምሥጢር የሠጠን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓሉን የሠላም የጤና የበረከት ያድርግልን አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

 

ማሳሰቢያ

ዘወትር እሁድ ጸሎተ ኪዳን፤ ስርዓተ ቅዳሴ እና ልዩ ስዩ መርሐግብሮች ስለሚኖረን በሰዓቱ ተገኝተን የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን

ሰዓት፡ ከጠዋቱ 07፡00 - 12፡00

ቦታ፡
Bjorknåskyrkan
Vårmdovågen 622

ጥቆማ፡
ከ Slussen Buss 444, 422 ወይም 471 ይዘው Centeralplan ላይ ይውረዱ።

ግጻዌ

በፌስ ቡክ ያግኙን